የቤት ሽያጭ የመንደር ውል በሕግ ፊት የሚፀና መሆን አለመሆን (Validity of Unauthenticated and Unregistered Contract of Sale of a House)

Authors

  • Dr. Dejene Girma Ethiopian Civil Service University

Abstract

ውል በየእለቱ የሚፈፀም እና ለሰው ልጅ ህይወት አስፈላጊ የሆነ ኩነት ነው፡፡ ሰዎች የሚፈፅሟቸው በርካታ
ተግባራት ከውል ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ሁሉም የሚፈፀሙ ውሎች በህግ ፊት ተቀባይነት
እንዲኖራቸው የሚያደርጓቸውን መስፈርቶች የሚያሟሉ ናቸው ሊባል አይችልም፡፡ አስፈላጊውን ህጋዊ
መስፈርቶች የሚያሟሉ ውሎች በህግ ፊት የሚፀኑ (valid) ውሎች ተብሎ የሚታወቁ ሲሆን መስፈርቶቹን
የማያሟሉ ውሎች ደግሞ በህግ ፊት የማይፀኑ (invalid) ውሎች ናቸው፡፡ በህግ ፊት የማይፀኑ (invalid)
ውሎች እንደ ሁኔታው ሊሰረዙ/ሊፈርሱ የሚችሉ (voidable) ውሎች ወይም ፈራሽ (void) ውሎች ሊሆኑ
ይችላሉ፡፡ ሊሰረዝ የሚችል ውል ከተፈፀመ ውሉ በፍ/ቤት እስኪፈርስ ድረስ ፍሬ የሚያፈራ ውል ይሆናል፤
ፈራሽ ውል ግን ከጅምሩ ሞቶ የሚወለድ ውል በመሆኑ አንዳችም ፍሬ አያፈራም፡፡ በሀገራችን ውሎች በህግ
ፊት የፀኑ እንዲሆኑ መሟላት የሚገባቸው መስፈርቶች ምን እንደሆኑ የተገለፀ ቢሆንም የየትኞቹ መስፈርቶች
አለመሟላት ውልን ሊሰረዝ የሚችል እና ፈራሽ ውል እንደሚያደርግ በግልፅ ተለይቶ አልተጠቀመጣም፡፡
በመሆኑም በህግ ፊት የማይፀኑ ውሎችን ሊሰረዙ የሚችሉ ውሎች እና ፈራሽ ውሎች ብሎ መለየት የሚቻለው
በዋናነት በህግ ትርጉም ላይ በመመስረት ነው፡፡ ለምሳሌ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል በፅሁፍ
ካልተደረገ በስተቀር ህጋዊ ውጤት አይኖረውም ተብሎ በፍ/ብሄር ህግ ተደንግጓል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ
የቤት ሽያጭ ውል ስልጣን ባለው አካል ካልተረጋገጣና ካልተመዘገበ በስተቀር ህጋው ውጤት እንደሌለው
አዋጅ ቁጥር 922/2008 ይደነግጋል፡፡ ይህ በቃል የሚደረግ ወይም በመንደር የሚደረግ የቤት ሽያጭ ውል
ፈራሽ ውል እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ከምዝገባ ጋር ተያይዞ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር
ችሎት በፅሁፍ የተደረገ የቤት ሽያጭ የመንደር ውል በተዋዋዮች መኖሩ እስካልተካደ ድረስ ህጋዊ እና ውጤት
ያለው ነው በማለት አስገዳጅ የህግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ይህ የሰበር ችሎት አቋም አዋጅ ቁጥር 922/2008
በአንቀፅ 9(1)(ሀ) ስር ከያዘው አቋም ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ በአንድ በኩል ሰዎች የመንደር ውል
በመጠቀም መንግስት ማግኘት ያለበትን ገቢ ለማሳነስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመቀነስ አዋጁ በግልፅ
እንደሚያስቀምጠው የመንደር ውል ፈራሽ ነው ብሎ አቋም መያዝ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል
አብዛኛውን ጊዜ የመንደር ውል የተዋዋይ ወገኖች ትክክለኛ ሀሳብ እና ፍላጎት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ
በአዋጅ ቁጥር 922/2008 አንቀፅ 9(1)(ሀ) ስር “ህጋዊ ውጤት አይኖረውም” የሚለው አገላለፅ እንደ
አስፈላጊነቱ ውል ሊፈርስ እንደሚችል የሚጠቁም ነው ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ ይህ አቀራራብ የአዋጁ እና
የሰበር ችሎቱ አቋም እንዲጣጣም የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለወደፊት የሰበር ችሎቱ አስገዳጅ የህግ
ትርጉም ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በፀሃፊ እይታ ግን ከአዋጁ ዓላማዎች መካከል አንዱ ህጋዊነትን
ማረጋገጥ ስለሆነ ሰዎች የቤት ሽያጭ ውል እንዲረጋገጥና እንዲመዘገብ የማድረግ የህግ ግዴታ ተጥሎባቸው
እያለ ያንን ሳያደርጉ መቅረታቸው ውላቸውን ውጤት አልባ ሊያደርግባቸው ይገባል የሚለው አቋም የበለጣ
ህግ አክባሪነትን የሚያበረታታ ነው የሚል ነው፡፡ በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 922/2008 አንቀፅ 9(1)(ሀ) ስር
“ህጋዊ ውጤት አይኖረውም” የሚለው አገላለፅ “ፈራሽ” ነው የሚል መልዕክት ያስተላልፋል ተብሎ መወሰድ
አለበት፤ የሰበር ችሎቱም ለወደፊ ተመሳሳይ ጉዳይ ሲያገጥመው ከፍ/ብር ህጉ ድንጋጌዎች በተጨማሪ
የአዋጁንም ድንጋጌ ከግምት ውስጥ በማስገባት የህግ ትርጉም መስጠት ይኖርበታል፡፡

Author Biography

Dr. Dejene Girma, Ethiopian Civil Service University

Assistant Professor, School of Law, Ethiopian Civil Service University

Published

2024-08-28

Issue

Section

Ethiopian Journal of Legal Studies